Fana: At a Speed of Life!

እንግሊዝ ባለሃብቶቿን ከኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ አምራቾች ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች መሆኗን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ ባለሃብቶችን ከኢትዮጵያ አምራቾች ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር  አንጌላ ሬይነር ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ጋር በሐዋሳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ዋና ስራ አስፈፃሚው ፥ ኮርፖሬሽኑ የሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ለአካባቢ ጥበቃ ስራ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በእያንዳንዱ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ ለአካባቢ ብክለት ምክንያት የሚሆኑ የፋብሪካ ፍሳሾችን የሚያጣሩ የፍሳሽ ማጣሪ ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አንጌላ ሬይነር በበኩላቸው ÷በእስያ የሰራተኞች ደሞዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ አምራቾች የአፍሪካ ገበያን ቀዳሚ ምርጫቸው እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ አልባሳት እና ጨርቃጨርቅ አምራቾች መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሯ ÷ የእንግሊዝ ባለሃብቶችን ከኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች ጋር ለማስተሳሰር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከር በእንግሊዝ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላትን ከእንግሊዝ ባለሃብቶቸ ጋር በማስተሳሰር ሊሰራ የሚችልበትን አጋጣሚ ማየት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያና እንግሊዝ አጋርነት ከፖለቲካ እና ከዲፕሎማሲ በላይ በከፍተኛ የንግድና የኢኮኖሚ ትብብርን ሊጠናክር እንደሚገባ መግለፃቸውን ከኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.