ታጂኪስታን ኢትዮጵያ በቀጣናው እያበረከተችው ላለው አስተዋጽኦ ድጋፏን እንደምትቀጥል አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀጣናውን ብሎም አፍሪካን ከመካከለኛው ኤዥያ ጋር ለማቀራረብ የምታደርገውን ጥረት እንደምትደግፍ ታጂኪስታን አስታወቀች፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ለታጂኪስታን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኢሞማሊ ራህሞን አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ ትኩረት ያደረገችባቸውን ወቅታዊ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ክንውኖች አምባሳደሩ ለፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አቪዬሽን፣ ኢነርጂ፣ ደኅንነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጠንካራ የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ለመመስረት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና የባለብዙ ወገን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትፈልግም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ቀጣናውን ብሎም አፍሪካን ከመካከለኛው ኤዥያ ጋር ለማቀራረብ የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉም አስታውቀዋል፡፡