Fana: At a Speed of Life!

የንግድ ከባቢ ሁኔታን ማዘመን ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መሳካት ወሳኝ ነው – አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተተገበረ ለሚገኘው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መሳካት የንግድ ከባቢ ሁኔታን ማዘመን ወሳኝ ነው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

ሁለተኛው የንግድ ከባቢ ሁኔታ ምቹነት የሪፎርም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር የስትሪግ ኮሚቴ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና የስትሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት÷ሁለኛው የንግድ ከባቢ ሁኔታ ምቹነት የሪፎርም ሥራ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን አንስተዋል፡፡

ኮሚቴው በቆይታው የግሉ ዘርፍ ማነቆዎችን ለመለየትና ማሻሻያዎችን ለመቅረጽ የሚያስችል ጥናት መስራቱን ነው ያስረዱት።

የዛሬው ውይይትም በ2ኛው የንግድ ከባቢ ሁኔታ ምቹነት ሪፎርም የተለዩ ኢኒሼቲቮች በምን አይነት የአመራር ቁርጠኝነትና ቅንጅት ሊተገብሩ ይገባል በሚሉ አስቻይ ሁኔታዎች ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ሪፎርም ምዕራፍ 100 ኢኒሼቲቮችን ይዞ ወደ ተግባር መግባቱን አንስተው÷ከእነዚህ መካከልም 68ቱ በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቁና በንግድ ከባቢ ሁኔታ ላይ ለውጥ ማጣት የቻሉ ናቸው ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ግቡን እንዲመታ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ ለዚህም አጠቃላይ የንግድ ከባቢያዊ ሁኔታን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከፖሊሲ ተገማችነት፣ ከቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ፣ አዳዲስና ነባር ባላሃብቶቹን ወደ ዘርፉ ከማስገባት አንጻር የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ መስራት እንደሚገባ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ ፣ ኢንቨስመንትን የሚስብ፣ አዳዲስ የሥራ እድል የሚፈጥር፣ የተቀላጠፈና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት የሚሰጠበት ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.