የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አባላት ችግኝ ተከሉ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ ዑመርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሀገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም አካል አንድ የሆነው በክልሉ በአንድ ጀንበር ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ንቅናቄ ውስጥ ክልሉ 3 ነጥብ 8 ሚሊየን ድርሻ ወስዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ያሉት አቶ ሙስጠፌ እስከ ዛሬ 2 ሚሊየን 358 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ገልፀዋል።
ለመትከል የተቀመጠው እቅድ ለማሳካት የቀሩትን 1 ሺህ 441 ሺህ ችግኞችን በተቀመጠው ግዜ ሰሌዳ ዉሰጥ እንደሚተከሉ አሳውቀዋል።

ለዚህ ስኬት ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉ የክልሉ አመራሮችና ህዝብ ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።
የአረንጓዴ ልማት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ቀጣይነትና ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በየጊዜው የሚፈጠሩ የተፈጥሮ አደጋዎችን የሚቀንስ በመሆኑም ህብረተሰቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ በማቅረብ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ለኮሮና ቫይረስ በሚያጋልጥ መልኩ መሆን እንደሌለበት ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የጉባኤ አባላት የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የአረንጓዴ ልማት ስራ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ መትከል ብቻ ሳይሆን ማሳደግና መንከባከብ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡
ከህዝብና ከመንግስት የተሰጣቸውን አደራ ለመወጣት በማሰብ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማከናወናቸውን አመልክተዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የሚካሄደው ችግኝ ተከላ የክልሉን ደን ሽፋን የማሳደግ ጉልህ ሚና እንዲወጣ የጉባኤ አባላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ- ጉባኤ አቶ ላክዴር ላክባክ አሳስበዋል፡፡