የቬትናም እና ሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከቬትናም ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከሩሲያ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ከምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንጉዬን ሚንህ ሃንግ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል የኢንቨስትመንት ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም ንግድን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቬትናም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹት ፍጹም (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚያደርጉ የቬትናም ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
በተመሳሳይ የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ከሩሲያ የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ማክሲም ሬሼትኒኮቭ ጋር በተወያዩበት ወቅት፤ ሁለቱ ወገኖች የኢኮኖሚ ትሥሥራቸውን በይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ቱሪዝም እና ዲጂታል ኢኮኖሚ በመሳሳሉ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡