በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ለአካባቢው ልማት ትልቅ እገዛ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና በክልሉ ገጠር ቴክኖሎጂና ዘር ብዜት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ተገኝተው የልማትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ተመልክተዋል።
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ የተቀረጹ ፖሊሲዎች መሬት ላይ መውረዳቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡
የዘርፉ ተቋማት ችግር ፈቺ ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ ለአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የቴራዞን ምርት እያቀረበ የሚገኘው የአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በአሶሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና በክልሉ ገጠር ቴክኖሎጂና ዘር ብዜት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተመለከቷቸው ተግባራትም የአካባቢውን ልማት ለማሳለጥ እገዛ እያደረጉ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በክልሉ ያለውን ሊለማ የሚችል ጸጋ በአግባቡ ለማበልጸግ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የቴክኒክና ሙያ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አወሉ አብዲን ጨምሮ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) እና ሌሎች አመራሮች በቦንጋ ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡