የዓባይ ወንዝ የቀዳሚም ሆነ የወቅታዊ ግልጋሎት መብት የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም መብት የሚከለክል አለመሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓባይ ወንዝ ላይ ያለው የቀዳሚም ሆነ የወቅታዊ ግልጋሎት መብት የኢትዮጵያን በወንዙ የመጠቀም መብቷን የሚከለክል አለመሆኑ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የአባይ ወንዝ ተፋሰስ የህግ ማዕቀፍና የሃይድሮ ፖለቲክስ ዙሪያ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው።
በመድረኩ በቀረበ ጥናት መሰረት በአለም አቀፍ ህጎች መነሻ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት እንዳላት ነው።
ከ80 በመቶ በላይ የሆነው ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ እስካሁን ከ1 እስከ 2 በመቶ ብቻ ነው እየተጠቀመችበት የሚገኘው።
ለዚህም በታችኛው የተፋሰስ ሃገራት የተፈረሙ ስምምነቶች ማነቆ መሆናቸውን በውይይቱ ላይ “የዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም የህግና የፍትህ ጉዳዮች ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት ከፍተኛ የህግ ተመራማሪው ታደለ ተካ ተናግረዋል።
በተለይ በግብጽ በኩል የሚነሳው በውሃው ላይ ያላት ቀዳሚ ተጠቃሚነት በአለም አቀፍ ህጎች መነሻ ፍትሃዊነት እና ሚዛናዊነትን እስካላስጠበቀ ድረስ ተቀባነት የሌለው ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር እና በ1969 የጄኔቫ ኮንቬንሽን ላይ በተቀመጠው መሰረት ሁለት ወገኖች ባደረጉት ስምምነት 3ኛ ወገን ሆና በተደረጉ ስምምነቶች ልትገዛ አትችልም ተብሏል።
በሌሌች አለም አቀፍ ህጎችም መነሻ በሉዓላዊ ግዛቷ ባላት የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት አላት ተብሏል።
በ2004 በበርሊን ደንብ ላይ በተቀመጠው መሰረትም ወቅታዊ ግልጋሎት ህጋዊነቱ የሚረጋገጠው ፍትሃዊ እና ሚዛናዊነት ሲሆን ብቻ ነው ስለሚል፤ ይህ በተደጋጋሚ በግብጽ የሚነሳውን ቀዳሚ ግልጋሎት እና ወቅታዊ ግልጋሎት ተቀባይነት የሌለው ነው።
ከዚህም ባለፈ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት የመልማት መብቷን የሚጋፋ ስለሆነ የቀደመው አካሄድ ተቀባይነት የሌለው ነው።
ከዚህም በመነሳት በዓባይ ወንዝ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር በተለይ የናይል ቢዚን ኢኒሼቲቭን በማጠናከር ስምምነቱን ከፈረሙ 6 ሃገራት መካከል ተጨማሪ ሃገራት ስምምነቱን እንዲያጸድቁ የማድረግ ስራ ልትሰራ ይገባል ተብሏል።
በሌላ በኩል በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ከተደረጉ ስምምነቶች 60 በመቶዎቹ ስኬታማ ያልሆኑት በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ስለሆነ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ግብፅ መስራት ይኖርባታል ተብሏል።
በምስክር ስናፍቅ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።