Fana: At a Speed of Life!

ከደንበኞች ዕውቅና ውጭ ከሂሳባቸው ገንዘብ ተቀናሽ አድርጓል የተባለው ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከደንበኞች ዕውቅና ውጭ ከሂሳባቸው በመቀነስ ወደ ግል የቴሌ ብር አካውንቱ ሂሳብ አስተላልፏል የተባለው ተከሳሽ ሙሀመድ ኡስማን እንዲከላከል ብይን ተሰጠ።

በወጋገን ባንክ ገርጂ ሰንሻይን ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን የነበረው ግለሰብ፤ ከ14 ደንበኞች ላይ ገንዘብ በመቀነስ ወደራሱ አስተላልፏል በሚል በቀረበበት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ነው እንዲከላከል ብይን የተሰጠው።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ሆኖ እየሠራ ሳለ፤ የተሰጠውን ስልጣን እና ኃላፊነት ያለአግባብ በመገልገል፣ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የባንኩን የሀብት ማሰባሰብ እና የቅርንጫፍ ባንክ አሠራር መመሪያን በመተላለፍ ወንጀሉን መፈፀሙን የቀረበበት የመጀመሪያ ክስ ያሳያል።

የባንኩን የኮር ባንኪንግ ሲስተም በመጠቀም ያለ ሂሳቡ ባለቤቶች ዕውቅና በራሱ አዘጋጅነትና አፅዳቂነት ከግንቦት 5 ቀን እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ከ14 የባንኩ ደንበኞች የተለያየ መጠን ያለው ብር ወደራሱ የቴሌ ዋሌት ማስገባቱን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በዚህም 191 ሺህ 600 ብር ከ14 ደንበኞች ዕውቅና ውጭ ከሂሳባቸው በመቀነስ ወደ ራሱ የቴሌ ብር ዋሌት በማስተላለፍ ገንዘቡን መውሰዱ፤ የተሰጠውን ኃላፊነትም አላግባብ በመጠቀም በፈፀመው ከባድ የሙስና ወንጀል መከሰሱ ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ተከሳሹ በባንኩ የደንበኞች አገልግሎት መኮንን ሆኖ እየሠራ ሳለ፤ በግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም የዕለቱን ሥራ ለማከናወን ከባንኩ ገንዘብ ያዥ 151 ሺህ 20 ብር ከተረከበ በኋላ ሂሳቡን ሠርቶ ሲጨርስ ቀሪውን ጥሬ ገንዘብ ማስረከብ ሲገባው ገንዘቡን ሳያስረክብ ሥራውን በመሀል አቋርጦ በመሄድ በተደረገው የገንዘብ ቆጠራ ከተረከበው ገንዘብ 40 ሺህ ብር ቀንሶ በመውሰድ ያጎደለ በመሆኑ በሕዝባዊ ድርጅት ላይ በፈፀመው ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ሁለተኛ ክስ በዐቃቤ ሕግ ተመስርቶበታል፡፡

በዚህም ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉን ያስረዱኛል ያላቸው ሰባት የሰው እና የሠነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፤ ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰውና የሠነድ ማስረጃዎች መርምሯል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ላይ እንዲከላከል ዛሬ በዋለው ችሎት ብይን የሰጠ ሲሆን፤ የተከሳሹን የመከላከያ ምስክሮች ቃል ለመስማትም ለሚያዝያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በመቅደስ ከበደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.