የጋምቤላ ክልል መንግስት ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል መንግስት ካቢኔ በዛሬው ዕለት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በዚህ መሰረትም ካቢኔው የጋምቤላ ክልል አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
የጋምቤላ ክልል የመንግስት ልማት ድርጅት ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉም ተመላክቷል፡፡
ካቢኔው የጋምቤላ ክልል መንግስት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር አገልግሎት ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን÷የተሻሻለውን የጋምቤላ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ አዋጅም አጽድቋል።
በተጨማሪም ካቢኔው የዓሳ ሃብት ጥበቃ አስተዳደርና ግብይት ቁጥጥር ደንብ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡