ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባሕር ዳር ኮሪደር ልማት ሥራን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባሕርዳር ከተማ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን ወደ ከፍታ በሚወስድ ሥራ ላይ ትገኛለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እንደጎበኙ አንስተዋል፡፡
ባሕር ዳርን ወደ ስማርት ሲቲ ለማሸጋገር ከሚረዱ ተግባራት መካከል አንዱ የሆነውን የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በፍጥነት ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራዎች የጣና ሐይቅና የዓባይ ወንዝ መናገሻ የሆነችውን ባሕር ዳር ይበልጥ የውበት ግርማ እንደሚያላብሱ አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የከተማዋን የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት መዳረሻነት ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ከምንም በላይ በኮሪደር ልማት እየዋሉ ያሉ አስፈላጊ ግብዓቶች በአብዛኛው በክልሉ የሚመረቱ መሆናቸው ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።