በትግራይ ክልል በጥንታዊ ቅርሶች ላይ የዕድሳትና ጥገና ስራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች ላይ የዕድሳት እና የጥገና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
በክልሉ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የታነጹ ጥንታዊ ኪነ ህንጻዎች፣ ቅርሶች እና ሌሎችም የቱሪዝም መስህብ ታሪካዊ ሥፍራዎች ጥገና እና እድሳት እየተደረገላቸው መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አጽብሃ ገብረ እግዚአብሄር (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት አስር የሚደርሱ ጥንታዊ ገዳማት፣ አብያተ-ክርስቲያናት እና ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎች በባለሙያዎች ተጠግነው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ገልፀዋል።
የየሃ ጥንታዊ ቤተ መንግስት፣ የአልነጃሺ መስጊድ እና የአክሱም ሃውልት በውጭ ሕንጻ ተቋራጮች አማካኝነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የጥገና ሥራቸው እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው፤ በክልሉ የሚገኙ አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች የባለሙያ ድጋፍ በመስጠት አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን የመጠገን፣ የመጠበቅና የማስተዋወቅ ስራ ማህበረሰብ ተኮር የቱሪዝም ልማትን ለማስፋፋትና የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ፍሰት ለመጨመር እንዳስቻለም አመልክተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።