የብልጽግና ፓርቲ የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በዋና ጽሕፈት ቤቱ ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ፤ አጠቃላይ ሀገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ጠንካራ ፓርቲ ግንባታ ለማሳካትና በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት የሚሠሩ የንቅናቄ አጀንዳዎች ግምገማ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ባደረጉት ንግግር፤ የፓርቲ መደበኛ ሥራዎች፣ የኢንስፔክሽንና ሥነ-ምግባር ኮሚሽን ግብረ መልስ እና በየክልሉ ያሉ የፖለቲካ አዝማሚያ ግምገማ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጉባዔ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች አፈጻጸም በተመለከተም ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት የሚሠሩ የንቅናቄ ሥራዎች አፈፃፀም ግምገማ እንደሚደረግ መገለጹን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚከናወኑ ሥራዎች እና ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ያሉበት ደረጃ በስፋት እንደሚገመገምም አቶ አደም አስረድተዋል፡፡