የአርብቶ አደሩን የእንስሳት ኢንሹራስ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርብቶ አደሩን የእንስሳት ኢንሹራስ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴሩ የአርብቶ አደር የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ጀማል አልዬ÷ በ2ኛው የእንስሳት ኢንሹራንስ ምዝገባ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የአርብቶ አደሩ አካባቢ በተደጋጋሚ በድርቅ አደጋ የሚፈተን በመሆኑ የአርብቶ አደሩ የኑሮ መሰረት የሆኑት እንስሳት ለችግር ሲጋለጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሚተገበሩ ቁልፍ ተግባራት መካከልም የእንስሳት ኢንሹራንስ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አርብቶ አደሩ የኢንሹራንሱ ተጠቃሚ እንዲሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በትስፋት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
አገልግሎቱ አርብቶ አደሩ ሃብቱን ወደ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓት በማስገባት ተጠቃሚነቱንና ዋስትናውን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚያስችል ነው ያስረዱት፡፡
በድርቅ ወቅት እንስሳቱ እንዳይጎዱና እንዳይሞቱ የመኖ፣ የመድሃኒት፣ የውሃና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን ለአርብቶ አደሩ እንደሚያቀርብም አብራርተዋል።
በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እየተተገበረ ያለው የእንስሳት ኢንሹራንስ 2ኛ ዙር ምዝገባ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሳምንታት እንደቀሩት አንስተዋል፡፡
ስለሆነም አርብቶ አደሩ በቀሩት ሳምንታት ኢንሹራንሱን በመመዝገብ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።