ኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን በማገት ሊብሬውን በመቀየር መኪናውን ሊነጥቁ ነበር የተባሉ 5 ተከሳሾች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት ሊብሬውን በመቀየር መኪናውን ሊነጥቁ ነበር የተባሉ 5 ተከሳሾች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡
የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ 1ኛ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣ 2ኛ የኡስታስ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ እና በአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ ልየው አሰፋ እና ዓለሙ ኦልጅራ ናቸው።
ተከሳሾቹ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሃመድ የሆነውንና የዋጋ ግምቱ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቪ8 ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ማህደሩን በመለወጥና በሽያጭ በማስተላለፍ ለመውሰድ ሲሉ መያዛቸው ተመላክቷል፡፡
በዚህም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት በተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ያስተላለፈ ሲሆን÷ተከሳሾቹም የቅጣት ማቅለያ ያሉትን ነጥብ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡
ተካሳሾቹ የቤተሰብ አስተደዳሪ መሆናቸው፣ ማህበራዊ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ፣ መልካም ሥነ-ምግባር እንዳላቸው፣ በተለያዩ የልማት ሥራዋች ላይ እንደሚሳተፉ እና የሕክምና ክትትል እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች መርምሮ ተከሳሾቹን በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
በዚህ መሰረትም 1ኛ ተከሳሽ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በ4 ዓመት ጽኑ አስራት እና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በተጨማሪም 2ኛ፣ 3ኛ፣4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ከተያዙበት ቀን ጀምሮ እያንዳንዳቸው በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራትና በ2 ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡
በመቅደስ የኔሁን