የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እየተከበረ ነው፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሎሚ በዶ በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ ተከብሯል፡፡
በዚሁ ወቅት ምክትል አፈ-ጉባዔዋ፤ በድሬዳዋ አሥተዳደር ሴቶችን ለማበረታት የተከናወኑ ተግባራት ጎብኝተዋል፡፡
በዕለቱም የሴቶች ቀን አስመልክቶ በሴት ኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር መከፈቱን አሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ደሴ ከተማ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ተክብሯል፡፡
በአከባበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)÷ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።
በደሴ ከተማ ሴቶችን ለማበረታት የተከናወኑ ተግባራትን ያደነቁት ኃላፊዋ፤ በቀጣይም ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲጥሉ አሳስበዋል፡፡
በከድር መሀመድ