የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በ7 አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ካቢኔ ባካሄደው 4ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በሰባት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚሁ መሠረት አንደኛ፤ ሀገራዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳ ላላቸው የማኑፋክቸሪንግ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የሚውል የቦታ ጥያቄን መርምሮ ማጽደቁ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም፤ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ ይረዳ ዘንድ የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን ተወያይቶ ማጽደቁን የአሥተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በምሽት የንግድ ቤቶች እና የትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ለማራዘም በወጣው ደንብ ዝርዝር ላይ ተወያይቶ አጽድቋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የተርሚናል አገልግሎት አሠራር እና ቁጥጥር ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ አፅድቋል::
ሌላኛው ካቢኔው ተወያይቶ ያጸደቀው አጀንዳ፤ የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ አደረጃጀት እና አሠራርን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡
የመብራት አገልግሎት አሥተዳደር ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 166 / 2016 ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁም ተጠቅሷል፡፡
በመጨረሻም የገርቢ የመጠጥ ውኃ ግድብ ፕሮጀክት ለመተግበር የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል ነው የተባለው፡፡