Fana: At a Speed of Life!

ነጋችንን የምንገነባው ባህልና ወጎቻችንን በአግባቡ መንከባከብና ማጎልበት ስንችል ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነጋችንን የምንገነባው ባሕልና ወጎቻችንን በአግባቡ መንከባከብና ማጎልበት ስንችል ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

72ኛው ዙር የቦረና አባ ገዳ ባሊ (ሥልጣን) ርክክብ ሥነ-ሥርዓት ባሕልና እሴቱን በጠበቀ መልኩ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

በዚህም የ71ኛው ዙር አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ ለ72ኛው አባ ገዳ ጉዮ ቦሩ ጉዮ ሥልጣናቸውን ባማረ መልኩ አስረክበዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ÷የገዳ ሥርዓት በሕዝቡ ባህልና እሴቶች ታንፆ እና በሂደት ያጋጠሙ ችግሮች በጥናት በማስተካከል እዚህ መድረሱን አንስተዋል፡፡

“ነጋችንን የምንገነባው ባሕልና ወጎቻችንን በአግባቡ መንከባከብና ማጎልበት ስንችል ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ትውልዱ ዘመኑን በዋጀ ሁኔታ ወጉንና ባህሉን በማደስ አጎልብቶ ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

“የክልሉ መንግሥትም ይኸን መሠረት በማድረግ በሥርዓተ ትምህርትና በቴክኖሎጂ ግንባታ እንዲሁም በማህበራዊውና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሒደት ውስጥ የሕዝቡን ባህልና ወግ መሠረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል” ብለዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው ÷”የገዳ ሥርዓት በዘመናት የስልጣኔ ሂደት ሁሉ ራሱን እያደሰ እና ፈተናዎችን እያለፈ ባማረ መልኩ ለዚሀ በቅቷል” ብለዋል።

“ቦረና ገዳን እንደ ልጁ ተንከባክቦ ለዚህ አድርሷል” ያሉት ሃላፊዋ፤ “የገዳ ሥርዓት ትውልድን እየገነባ ያስቀጠለ በመሆኑ ለወፊቱም አምሮና ጎልብቶ ይቀጥላል” ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትም የገዳን ሥርዓት ትውልዱ እንዲማረውና ለዓለም እንዲተዋወቅ አጠናክሮ ይሰራል ” ሲሉ አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ የኬንያ ልዑካን ቡድን የተሳተፉ ሲሆን በኬንያ የማርሳቤት ካውንቲ ገዥ መሐሙድ ዓሊ ባስተላለፉት መልዕክት÷ “የዛሬው እለት የደስታ ቀን ነው፤ እኛም የወንድሞቻችንን ደስታ ለመካፈል መጥተናል” ብለዋል።

“የገዳ ሥርዓት ውብ ባህልና ጥንታዊ የዴሞኪራሲ ሥርዓት ነው” ያሉት ገዥው፤ ይኸንን ውብ ባህል ጠብቀው ያቆዩትን የፌደራልና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን አመስግነዋል።

ገዥው በስነ ስርአቱ ላይ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትን ማስተላለፋቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.