Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ በሀሰተኛ የብር ኖት እንዳይታለል ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ህብረተሰቡ በሀሰተኛ የብር ኖት እንዳይታለል በግብይት ወቅት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳሰበ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ በበዓል ወቅቶች የሚፈጸሙ የተለያዩ የማጭበርበር ወንጀል ድርጊቶች ከወትሮው ይጨምራሉ።

የ2017 የትንሳዔ በዓል በድምቀት እንዲከበር እና ህብረተሰቡ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊት እንዳይጋለጡ ለመከላከል ፖሊስ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸው፤ ህብረተሰቡም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከበዓሉ ጋር በተገናኘ የኤግዚቢሽን እና ባዛር ግብይቶች በብዛት ስለሚኖሩ ማህበረሰቡ በተለምዶ ‘ኪስ አውላቂ’ ከሚባሉ ሌቦች ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ጠቅሰው፤ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመለከትም ለጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ወንጀልን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

ለበዓል የሚቀርቡ ሸቀጦች ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅሎ የመሸጥ ድርጊት እንደሚፈጸም ገልጸው፤ ይህንን ለመከላከል በሰዋራ ስፍራ ግብይት ከመፈጸም መቆጠብ እንደሚገባ መክረዋል።

ገበያ ላይ ካለው ዋጋ እጅግ ያነሰ ክፍያም ሲጠየቁ ምርቱ ችግር ያለበት ወይም የተሰረቀ ሊሆን ስለሚችል መጠራጠር ተገቢነት እንዳለው አመልክተዋል።

ሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለመከላከል ክትትል እንደሚደረግ የገለጹት ኮማንደር ማርቆስ፤ በግብይት ወቅት በሀሰተኛ የብር ኖቶች ላለመጭበርበር ሸማቹም ሆነ ነጋዴው አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ሀሰተኛ የብር ኖቶች ወደ ገበያ የሚገቡት ከትክክለኛ የብር ኖቶች ጋር በመቀላቀል እና ሙሉ ለሙሉ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ብቻ በመጠቀም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የእንስሳት ግብይት ሲደርግ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን መጠቀም የሚመረጥ መሆኑንም መክረዋል።

ጠጥቶ ከማሽከርከር፣ ትርፍ ሰው ከመጫን እንዲሁም ከፍጥነት በላይ ከማሽከርከር መቆጠብ እንደሚገባ በመግለጽ፤ የትራፊክ ደንብን ማክበር ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.