በባህር ዳር ከተማ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የሚካሄደው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ ዛሬ ተጀምሯል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት የተጀመረው ፕሮጀክቱ 800 ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር ስፋት ያለው አስፋልት መንገድ እንደሆነ ተመላክቷል።
በማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓቱ ላይ መንገዱ ጣና ሀይቅን በቀጥታ ከከተማው የሚያገናኝ መሆኑ ተገልጿል።
ይህም የከተማዋን ውበት፣ የቱሪስትና የኢንቨስትመንት ማዕከልነት ይበልጥ የሚያሳድግ እንደሆነ ተነግሯል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የ3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ደረጃውን ጠብቆ እየተከናወነ ሲሆን ሲሆን በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
የኮሪደር ልማቱ የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የብስክሌት መንገድና ሌሎች ልማቶችን አካቶ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።