Fana: At a Speed of Life!

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 5 ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ በ33ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ዛሬ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።

በ54 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አስቶንቪላ በፒኤስጂ በድምር ውጤት ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከተሰናበተበት ጨዋታ መልስ የሚያደርገው ፍልሚያ ነው።

በ59 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ላይ የሚገኘው ኒውካስል ዩናይትድ በሁሉም ውድድር ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አልተሸነፈም።

ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ግንኙነቶች ኒውካስል ዩናይትድ ሶስቱን ሲያሸንፍ አስቶንቪላ በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ሲቲ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ኤቨርተንን ይገጥማል።

በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮን መድረክ ቦታ ለማግኘት እየተፋለመ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ በ55 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ማንቼስተር ሲቲ በሁሉም ውድድር ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።

ባለሜዳው ቡድን ኤቨርተን በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ በሶስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

በተመሳሳይ አመሻሻ 11 ሰዓት ላይ ብሬንትፎርድ ከብራይተን፣ ክሪስታል ፓላስ ከቦርንመዝ እንዲሁም ዌስትሀም ዩናይትድ ከሳውዛምፕተን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ሊጉን ሊቨርፑል በ76 ነጥብ ሲመራው አርሰናል በ63፣ ኒውካስል ዩናይትድ በ59 እንዲሁም ኖቲንግሀም ፎረስት በ57 ነጥብ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ወራጅ ቀጠናው ላይ ኢፕስዊች ታውን፣ ሌስተር ሲቲ እና አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው ሳውዛምፕተን ይገኛሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.