በዓሉን በመረዳዳት እና ማዕድ በማጋራት ማክበር ከሃይማኖቱ ተከታዮች እንደሚጠበቅ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ነገ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር፣ መረዳዳትና መተሳሰብ በላቀ ደረጃ የሚስተዋልበት ሃይማኖታዊ በዓል መሆኑን አውስቷል፡፡
ምዕመናን በዐቢይ ጾም ሲያከናውኗቸው የነበሩ በጎ ተግባራትን በትንሣኤ በዓልና ከዚያም በኋላ አጠናክረው እንዲያስቀጥሉም ጠይቋል፡፡
ትንሣኤ ከሕማማት እና ስቅለት ቀጥሎ በፅናት እና በመሥዋዕትነት በማለፍ የሚከበር በዓል መሆኑን ያወሳው አገልግሎቱ፤ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ሕማማትን ተሻግራ ወደ መንሠራራት እየገሰገሰች ትገኛለች ብሏል፡፡
ቀደምት ኢትዮጵያውያን ውድ ዋጋ ከፍለው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረው እንዳስረከቡን፤ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የልማት ውጥኖቿን እያሳኩ ወደ ከፍታዋ እያወጧት ትገኛለች ሲል ገልጿል፡፡
በዓሉን እንደተለመደው በመረዳዳት፣ በመተሳሰብና ዐቅመ ደካሞችን በማገዝ እና ማዕድ በማጋራት ማክበር ከሃይማኖቱ ተከታዮች የሚጠበቅ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡