የሩሲያ-ዩክሬን ሰላም ማረጋገጥ አሜሪካ በምትፈልገው ፍጥነት ሊከናወን እንደማይችል ሩሲያ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ-ዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው የሰላም ጥረት አሜሪካ በምትፈልገው ፍጥነት ሊሳካ እንደማይችል ሩሲያ ገልጻለች፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግጭቱን በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ጦርነቱ ውስብስብ በመሆኑ የሰላም ጥረቱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በሚፈልገው ፍጥነት ይሰምራል የሚል እምነት እንደሌላት ነው ሞስኮ የገለጸችው፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ጦርነቱን ለማስቆም ከዩክሬን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ሆኖም ከኬቭ በኩል የተሰጠ ምላሽ አለመኖሩን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ፔስኮቭ አክለውም፥ አሜሪካ የሰላም ሂደቱ በፍጥነት እንዲቋጭ ፍላጎት እንዳላት እንገነዘባለን፥ ነገር ግን የጦርነቱ መንስኤ እጅግ የተወሳሰበ በመሆኑ በአንድ ጀንበር መቋጨት አዳጋች ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ