በአፋር ክልል አስር ፋብሪካዎች በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ – አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆኑ አስር ፋብሪካዎች በአፋር ክልል በቅርቡ ተመርቀው ስራ እንደሚጀምሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በአፋር ክልል ከለውጡ ወዲህ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፥ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለክልሉ ኢኮኖሚ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።
ንቅናቄው በተለይም ክልሉ በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና ቱሪዝም ዘርፎች ያለውን ትልቅ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የሆኑና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አስር ፋብሪካዎች በቅርቡ ተመርቀው በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንደሚገቡም ገልጸዋል።
ክልሉ ያለውን የጨው ሃብት ወደ ጥቅም በመቀየር ከውጭ ይገባ የነበረውን የጨው ምርት ሙሉ ለሙሉ መተካት መቻሉንም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።
የጨው ምርትን በጥሬ ከማምረት በዘለለ እሴት በመጨመር የተለያዩ ኬሚካሎችን ለማምረት የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው÷ ይህም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሒደቱን ያፋጥናል ብለዋል፡፡
የግብርና ምርታማነትን ከንቅናቄው ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በክልሉ በፍራፍሬ ምርት አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአፋር ክልል ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ከ300 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በ2014 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።