የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል መመሪያ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛ እና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ 1050/2017 ሆኖ ጸድቋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አማካሪ ከድልማግስት ኢብራሂም፤ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መቀየርን አስመልክቶ ለዘርፉ የስራ ሀላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የሰሌዳ ለውጡ ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ታሳቢ ያደረገ ሰሌዳ እንዲኖር ለማስቻል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነበረው የአሰራር ክፍተት፣ የሀብት ብክነት፣ በሲስተም የተደገፈ ስራ አለመኖር፣ የተላላፊና ቋሚ ሰሌዳ ለሀሰተኛ ሰሌዳ ሥራ የተጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንዲሁም የተሸከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ አመራረትና ስርጭት እና የአወጋገድ ችግር የሰሌዳ ለውጡን ማድረግ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸው፤ መመሪያው ችግሮቹን እንደሚፈታ አመልክተዋል።
መመሪያው በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፤ በተመዘገቡና ለምዝገባ በሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች፣ በተሽከርካሪ አምራች /አስመጪ/ገጣጣሚ ድርጅቶች፣ በተሽከርካሪ መዝጋቢ አካላት እንዲሁም በኢትዮጵያ በሚገኙ እና አህጉር አቀፍ ተቋማት እና በግለሰቦች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል።
በመሳፍንት እያዩ