Fana: At a Speed of Life!

አዲሱን ዓመት ከስጋት የጸዳ ለማድረግ የነሐሴን ወር በጥንቃቄ ማለፍ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) መጭውን አዲስ አመት ከስጋት የጸዳ እና የተሻለ አመት ለማድረግ የነሐሴን ወር በመጨረሻው የጥንቃቄ ደረጃ ማለፍ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

‘ማንም’ የተሰኘው ሃገር አቀፉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮቪድ19 የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄና ምርመራ ዘመቻ ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም መጭውን አዲስ አመት ከስጋት የጸዳ እና የተሻለ አመት ለማድረግ የነሐሴን ወር በመጨረሻው የጥንቃቄ ደረጃ ማለፍ ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም መንግሥት በቀጣይ የምርመራ አቅሙን በማሳደግ እንደሚሠራ ጠቅሰው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 91 በመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት ያልታየባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አሁን የተጀመረው የምርመራ ዘመቻ በርካታ ኮሮና ቫይረስ ያለባቸውን ሰዎች ለመለየት ያግዛልም ነው ያሉት።

በውይይቱ የላቦራቶሪ እና የማቆያ ቦታዎች እጥረት፣ የቤት ውስጥ ማቆያ፣ በድንበር አካባቢ ላይ ያሉ ተጽዕኖዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል።

በሃር አቀፉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ንቅናቄና የምርመራ ዘመቻ በቀጣዮቹ ሁለት ሣምንታት 200 ሺህ ሰዎችን ለመመርመር እንዲሁም 17 ሚሊየን ዜጎችን ቤት ለቤት ለመለየትና ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል።

በዘመቻው የሚገኘው ውጤት በቀጣዩ ዓመት ለሚከናወኑ ተግባራት አመላካች መነሻዎችን እንደሚሰጥና በተለይ ተማሪዎችና መምህራን በዘመቻው በመሳተፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱም መልዕክት ተላልፏል።

የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የማኅበረሰብ መሪዎች ለዘመቻው መሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

የክልሎች ፕሬዚዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በንቅናቄና በምርመራ ዘመቻው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል።

በትእግስት አብርሃም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.