Fana: At a Speed of Life!

በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ግዳጆችን እንደየአመጣጣቸው መመከት የሚችል ሠራዊት ተገንብቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ተገማችም ሆነ ኢ-ተገማች የሆኑ ግዳጆችን እንደየአመጣጣቸው መመከት የሚችል ሠራዊት ተገንብቷል ሲሉ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ።

በወቅታዊ የመከላከያ ሠራዊት ግዳጅ አፈጻጸም ላይ ማብራሪያ የሰጡት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንደተናገሩት፤ በአንድ ጊዜ መልከ ብዙ ግዳጆችን መወጣት የሚችል ሠራዊት ተገንብቷል።

በዝግጅት፣ በውጊያ እና በማድረግ አቅም በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ ተገማችም ሆነ ኢ-ተገማች የሆኑ ግዳጆችን እንደየአመጣጣቸው መመከት የሚችል ሠራዊት ነው የተገነባው ብለዋል።

በዚህም ከለውጡ በኋላ በሰው ኃይሉ፣ በአደረጃጀቱ እና በትጥቁ ኢትዮጵያን የሚመጥን ሠራዊት እንዲሆን ተደርጎ መሰራቱን ተናግረዋል።

ለቀጣናው መረጋጋትም የበኩሉን ሚና የሚጫወት ሠራዊት መሆኑን በመጥቀስ፤ ተደጋጋሚ ፈተናዎችን በድል መወጣቱን አብራርተዋል።

ህዝብና መንግስት የሚኮሩበት ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ በሰላም እጦት እንዳይደናቀፍ ያሻግራል ብለው የመጨረሻ ምሽጋቸው አድርገው የሚቆጥሩት ሠራዊት መሆን ችሏል ሲሉ አብራርተዋል።

ሠራዊቱ በመተካካት ሂደት ዓለም አቀፍ አሰራርን በመከተል በግልጽ በተቀመጠ መስፈርት ግዳጅን ለመወጣት ብቁ አባላትን እንደሚመለምል አስረድተዋል።

ከድሮን አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሠራዊቱ ላይ የሚነሱ ውንጀላዎች መሰረት የሌላቸው መሆናቸውን የገለጹት ኮሎኔል ጌትነት፤ እኛ ድሮን ስንል እና ጠላት ድሮን ሲል እንግባባለን ብለዋል።

ድሮን ለይቶ እየመታው እንዳለ የሚያውቀው ጠላት ርምጃው እንዲቆምለት ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሃይል ትምህርት እንዲቋረጥ መምህራንን እና ተማሪዎችን እየገደለ ትምህርትን አስቁሞ ድሮን መታ የሚለው ትምህርት ቤት ላይ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ትምህርትን አስቁሞ ትምህርት ቤት ተመታ ማለት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸው፤ ውሸት የማይሰለቸው ቡድን በአንድ ወቅት ድሮን ከእነፓይለቱ መትተን ጣልን ያለ ነው ሲሉ አስታውሰዋል።

ጽንፈኛው ቡድን ድሮንን ከሰሞኑ አጀንዳ አድርጎ ያመጣው ቡድኑ እርስ በርስ መወነጃጀልና መገዳደል እንዲሁም የብርቱካን ሀሰተኛ ዶክመንታሪን ጨምሮ ድርጊቱ መጋለጥ በመጀመሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጽንፈኛው ዓላማ የሌለውና ህዝብን ጠላት አድርጎ እየበደለ መሆኑን ገልጸው፤ የኢኮኖሚ ጥቅሙን ለመሙላት ለህዝብ ቆሜያለሁ ማለት አይሰራም ብለዋል።

የሰላም እጦት በተከሰተባቸው አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱ እየፈጸመ ባለው ህግ የማስከበር ተልዕኮ፤ ከህዝብ፣ ከመንግስት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በተከፈለው መስዋዕትነት፣ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸዋል።

በርካታ ታጣቂ ሃይሎችም የሰላም አማራጭን ተቀብለው መግባታቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.