Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሁል ጊዜ ስራችን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ አባቶቻችን በአርበኝነት ስሜት የኢትዮጵያን አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሁል ጊዜ ስራችን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምሥረታ ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለተቋም 116 አመታት ማለት ቀላል ትርጉም የሚሰጠው እንዳልሆነ ገልጸው፥ ቀጣይነት ያለው ሪፎርምና ዘመንን የሚዋጅ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት አመታት በኢትዮጵያ የተቋም ግንባታ በሰላምና ደህንነት ጠባቂ ተቋማት ላይ የተሰራው ስራ አመርቂ ቢሆንም፥ አሁን ዓለም ካለበት ሁኔታ አንጻር በቀጣይነት መሰልጠንና መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

የጸጥታ ተቋማት አሁን ላይ በተገኘው አኩሪ ውጤት ሳይዘናጉ በቀጣይነት አቅም መገንባትና ራሳቸውን ማሳደግ ላይ በጋራ እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ሰላምና አንድነት የማረጋገጥ ስራ ከፖሊስ ሰራዊቱ እንደሚጠበቅ አስገንዝበው፥ አንድ መሆን ከቻልን የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ብልጽግና ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል፡፡

የጠላቶቻችን ፍላጎት እኛን መለየትና መበተን በመሆኑ፥ የእኛ ዓለማ ብሔራዊ ፍላጎቶቻችንን አንጥረን ማወቅ፣ ሰላማችንን መጠበቅ፣ ተባብረን መትጋትና ከወንድም የጎረቤት ህዝቦች ጋር በጋራ መስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚያ ያለፈ ነገር ካለ እንደ አባቶቻችን በአርበኝነት ስሜት የኢትዮጵያን አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የሁል ጊዜ ስራችን ነው ሲሉ ለሰራዊቱ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት የማይፈልጉ ሀይሎች በተለመደው መንገድ በክንዳችን ይፈርሳሉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.