6ኛው የኮሜሳ ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን የንግድ ትርዒት ነገ ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ነጋዴ ሴቶች ፌዴሬሽን የንግድ ትርዒት ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
እስከ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው የንግድ ትርዒት ላይ ከ21 የኮሜሳ አባል ሀገራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ሴት ስራ ፈጣሪዎችና ነጋዴዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና በኮሜሳ ትብብር የተዘጋጀው 2ኛ የኮሜሳ ተቋማት ግንዛቤ ማስጨበጫ ፎረም በትናንትናው ዕለት ተጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
መድረኩ እንደ አህጉር አዳዲስ የቢዝነስ እይታዎችን በማበረታታት ቀጣይነት ያለው ንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።
ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ላይ በመሳተፍ የተለያዩ ልምዶችን እየተለዋወጡ እንደሚገኙም ተገልጿል።
መድረኩ የሴት ነጋዴዎችንና ሥራ ፈጣሪዎችን አቅም ለማጎልበትና እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።
በዘቢብ ተክላይ