ፖሊስን በቴክኖሎጂ ለማላቅና ለማዘመን በትኩረት እየተሠራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላምና የልማት ኃይል የሆነውን ፖሊስ በቴክኖሎጂ ለማላቅ፣ በሥልጠና ለማዘመን፣ የሥራ ቦታዎችን ምቹ ለማድረግና በሰው ኃይል ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ25ኛ ዙር ምልምል የፌደራል ፖሊስ ሰልጣኝ አባላት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች በሰላምና በሕግ አግባብ እንዲከናወኑ የሚያስችል ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ምቹ የመንቀሳቀሻ ሜዳ ለመፍጠር ፖሊስ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር÷ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌትና ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርዓያ ለመሆን የጊዜ ገደብና አቅጣጫ አስቀምጣ እየሠራች እንደምትገኝም ገልጸዋል፡፡
እነዚህ ርዕዮች ተሳክተው በመደመር መንገድ የብልጽግና ግብ ላይ ለመድረስ እንዲቻል ሰላማዊና ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ ሜዳ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፖሊስ በኢትዮጵያ ዕድገት ልክ በሥልጠና፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል በስልትና በመፈጸም አቅም ማደግ እንዳለበት ገልጸው፥ ይህንን ለማረጋገጥ መንግሥት የሪፎርም መርሐ ግብር ቀርጾ በትኩረት እየተገበረ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
በለይኩን ዓለም