በኦሮሚያ ክልል ከ250 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከ250 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
በቢሮው የአፈር ለምነትና ማሻሻያ ዳይሬክተር እሸቱ ለገሰ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በበጀት ዓመቱ የአፈር ለምነትን ለመጨመርና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
መደበኛ ኮምፖስትን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ለማዘጋጀት ከአርሶ አደሩ ጋር በትብብር መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም በ2017 በጀት ዓመት እስከ አሁን ከ250 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ መደበኛ ኮምፖስት መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም 3 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ቨርሚ ኮምፖስት እና ከ419 ሺህ ኩንታል በላይ ባዮስላሪ ኮምፖስት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሬት ጤንነትና አሲዳማነትን ለመከላከል ያለውን ጠቀሜታ አርሶ አደሩ በሚገባ መገንዘቡ ለዝግጅቱ መሳለጥ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አመልክተዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ሂደቱ እስከ ሰኔ ወር እንደሚቀጥል ገልጸው÷ አርሶ አደሩ የተዘጋጀውን ኮምፖስት በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ