Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለፁ።

6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በንግድ ትርዒቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ አፍሪካ በ2063 ለማሳካት ከያዘቻቸው አጀንዳዎች አንዱ የሴቶችን እኩልነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

የተቀናጀና የተናበበ ስራ ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የኮሜሳ መስራች አባሏ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ የፈጠረና ተወዳዳሪነትን ያሳደገ መሆኑንም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ኮሜሳ ለሴት ስራ ፈጣሪዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮሜሳ አባል ሀገራት ሴቶች በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሚገጥማቸውን ፈተናዎች ተቋቁመው በንግድ ሥራ ውጤታማ የሆኑ ሴቶች በርካታ መሆናቸውንም ነው የጠቀሱት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ውህደት በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለይታ ለመፍትሄው እየሰራች እንደሆነም ተናግረዋል።

የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የኮሜሳ አባል ሀገራት የበለጠ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሳልማ ማሊካ፤ በአፍሪካውያን መካከል የሚደረገውን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ውህደት ማፋጠን ይገባል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.