የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያሰባሰባቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ አስረከበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ለሀገራዊ ምክክሩ ግብአት የሚሆኑ አጀንዳዎችን አሰባስቦ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) አጀንዳዎቹን ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስካለ ለማ ተረክበዋል።
አጀንዳዎቹ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰቡና ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች እና በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ወ/ሮ አስካለ ለማ ገልጸዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሚናውን ሲወጣ የቆየው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን በቀጣይም ለልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መረጋገጥ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ መሰረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች የሚታዩ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባት መንስኤዎችን ለመለየት የሚያስችል አጀንዳ በመቅረጽ ምክክር እንዲደረግባቸው የማድረግ ዓላማ አንግቦ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ልዩነት በተፈጠረባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኮሚሽኑ በተቋማትና በማህበረሰብ ክፍሎች ተደራጅተው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን በአግባቡ እንደሚጠቀምባቸውም አረጋግጠዋል።