Fana: At a Speed of Life!

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቋሚነት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቋሚነት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን የሚዲያ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በአንድ ጣራ ስር ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን የሚሰጠው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ ማህበረሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ በአንድ ቦታ እንዲያገኝ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል።

12 ተቋማት ተቀናጅተው ከ41 በላይ አገልግሎቶችን የሚሰጥበትን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ የጎበኙ የሚዲያ ባለሙያዎች፤ ጉብኝቱ ስለ አገልግሎቱ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እገዛ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቋሚነት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን
መገንዘባቸውን ገልጸው፤ በአገልግሎት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ እንደሚያስችልም አመላክተዋል።

መሰል የአገልግሎት ማዕከሎችን በማስፋትና በማጠናከር የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

መንግስት ህብረተሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በተቀላጠፈና ባጠረ ጊዜ ውስጥ ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሎች ለማስፋፋት እየተሰራ ሲሆን ባጠረ ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ተመላክቷል።

በታሪኩ ለገሠ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.