Fana: At a Speed of Life!

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም በማሟላት ለልጆቻችን ተረጂነትን ሳይሆን ሀብት ማውረስ ይገባናል – አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም በማሟላት ለልጆቻችን ተረጂነትን ሳይሆን ሀብት ማውረስ ይገባናል ሲሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከፋና ፖድካስት ጋር ቆይታ ያደረጉት ኮሚሽነሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሀብት እና ለማምረት የሚመች የአየር ፀባይ ቢኖርም በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡

ለዜጎቻችን ሌላ ደራሽ እየጠፋ ስለሆነ በራሳችን አቅም ድጋፍ እያደረግን ውጫዊ ድጋፍ ትርጉም በማይኖረው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ተረጂነት፣ ጥገኝነት እና ጠባቂነት የኛ የኢትዮጵያዊያን ባህል መሆን ስለማይገባው ታታሪነትን ባህል ማድረግ አለብን ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲ ላይ አንዱና ትልቁ ስራ ሀገር በቀል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ መንግስት የሚመራው እና በሀገር በቀል አቅም ምላሽ የሚሠጠው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ቀውስን ከማስተዳደር ይልቅ ስጋትን ማስተዳደር ላይ በመስራት እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አሰራሮችን የመዘርጋት ሥራ በማከናወን ከተረጂነት ለመውጣት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ማህበረሰቡ በራሱ የሚሸፍናቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ሰፊ የመስሪያ ቦታ እና ብዙ ወጣት ባለበት ሀገር መታወቂያችን ተረጂነት መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

በከተማ እና በገጠር ሴፍቲኔት በተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማምጣት መቻሉን ገልፀው፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ያሳየችው ዕድገት ፈጣን መሆኑን መግለፃቸውን አንስተዋል።

ማህበረሰቡን ከዘላቂ ልማት ጋር በማስተሳሰር ከተረጂነት መውጣት የሚቻል በመሆኑ ሀገራዊ የሆነ ዕቅድ ተይዞ በመንግስት ቁርጠኝነት ከተረጂነት ለመውጣት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

የትኛውም ድጋፍ የሚሻ ዜጋ ሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት እንዳለው ገልጸው፤ ድጋፍ የሚደረገው በልዩ ሁኔታ ለመጥቀም ሳይሆን የመንግስት ግዴታም ስላለበት ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ሥራዎቻችንን ስንተገብር ጠባቂነትን ታሪክ በማድረግ ዘላቂ በሆነ መልኩ ከፈታን ሀገራዊ እንድምታው ከፍተኛ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡

ማንኛውም ዜጋ በተለያየ አጋጣሚ አደጋ ሊያጋጥመው ስለሚችል ሁሉም በዚህ ጉዳይ ላይ ቢተባበር ክብራችንን፣ ነፃነታችንን እና ሉአላዊነታችንን ማረጋገጥ እንችላለን ነው ያሉት፡፡

እርዳታ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ለማይመለከታቸው ሰዎች መበልፀጊያ እና የስለላ መሳሪያ ጭምር እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ሁላችንም ተረባርበን እና ተጋግዘን ለልጅ ልጆቻችን ተረጂነትን ሳይሆን ሀብትን ማውረስ ይገባናል ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.