የኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ በዲፕሎማሲ ተደማጭነቷን ከፍ አድርጓል – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ያከናወነቻቸው ሰፋፊ የተቋማት ግንባታ ሥራዎች በዲፕሎማሲ ተደማጭነቷ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ምሁራን ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ እየተጠናከረ በመጣው የተቋማት ግንባታ ሥራዋ ተፈላጊነትንና ተደማጭነትን እያተረፈች መሆኑን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ከኃይል አማራጭ ይልቅ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በባህል ትስስር በሁሉም ወገን የጋራ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተው ግንኙነቷ ውጤታማ መሆኗንም አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማትን ከማጠናከር ባሻገር በኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም በምግብ ራስን ለመቻል ያከናወነቻቸው ተግባራት ተጽዕኖዋን የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የታሪክና ባህል ተመራማሪው አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የተቋማት ግንባታ ሥራዎች ከፍ ባለ ደረጃ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ የተቋማት ግንባታ ሥራ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባሻገር ከሌሎች ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት በር የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለተጨቆነ ሕዝብ የነጻነት ምልክት መሆኗን አውስተው፤ የታሪክና የባህል ሀብቶቿን የዲፕሎማሲ አቅሟን በሚያጠናክር መንገድ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ