የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመድኃኒትነት የሚውሉ እጽዋትን በአግባቡ እየጠበቅሁ ነው አለ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመድኃኒትነት አገልግሎት የሚውሉ እጽዋትን በልዩ ትኩረት የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የመጠበቅና የማስፋፋት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታውቋል፡፡
በተለይም የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸው እጽዋት ከየም ብሔረሰብ ጋር የተለየ ቁርኝት ስላላቸው ሕብረተሰቡ ጭምር በአግባቡ ጥበቃ እንደሚያደርግ የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አድማሱ ወ/ማርያም ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ቢሮው የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸውን እጽዋት ጨምሮ በብዝኀ ሕይወት ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለአብነትም የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸውን እጽዋት በዘቦታ (በብዝኀ ሕይዎት ክምችት ቦታዎች) እና በመስክ ጂን ባንኮች የማቆየት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሥራው አበረታች ውጤት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በየም ዞን ፎፋ ወረዳ በ117 ሔክታር ላይ የብዝኀ ሕይዎት ክምችት መኖሩን እና ተከልሎ ሕብረተሰቡ በዓመት አንድ ጊዜ የመድኃኒት ለቀማ መርሐ-ግብር በማከናወን ተጠቃሚነቱ ከፍ እንዲል እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በ2 ነጥብ 5 ሔክታር ላይ የመስክ ጂን ባንክ በማቋቋም በርካታ የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸውን እጽዋት ከልሎ በመጠበቅ በአካባቢው ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በክልሉ ሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች የመድኀኒትነት ባህሪ ያላቸውን እጽዋት የመጠበቅ ሥራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ጤና ቢሮ ጋር በመሆን የማኅበረሰብ ነባር ዕውቀት በተደራጀ ሁኔታ እንዲጠና ብሎም የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸው እጽዋት በአግባቡ ለዘመናዊ ሕክምና ጥቅም እንዲውሉ ይሠራል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው