ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሯን ወደሌሎች ሀገራት እንድታስፋፋ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ወደ ሌሎች ሀገራት በማስፋፋት የአረንጓዴ ዐሻራ ዲፕሎማሲን ለማሳደግ እንድትጥር ተጠየቀ፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ ለዲፕሎማሲ ዘርፍ ተጨማሪ አቅም ከሚፈጥሩ ዘርፎች አንዱ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ያላት ልምድና ስኬት ተሰሚነቷን በይበልጥ እንደሚያሳድገው ጠቅሰው፤ በዘርፉ ያላትን ግምባር ቀደምነት ተጠቅማ ለገጽታ ግንባታ እንድትጠቀምበት መክረዋል፡፡
ይህን ውጤታማ ልምድ ለሌሎች ሀገራት ባካፈለች ቁጥር ወዳጅነትን በይበልጥ ለማጠናከር ይረዳታል ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በአኅጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወደስ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም በጉዳዩ ላይ ያላትን ልምድ ከማካፈል አልፋ አረንጓዴ ዐሻራ እንዲስፋፋ እየሠራች መሆኗን አስረድተዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ሰለሞን ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ስላላት በራሷ ወጪ በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን ለአጎራባች ሀገራት መለገሷን አንስተዋል፡፡
የተለያዩ ሀገራት መሪዎች እና ባለስልጣናትን ጨምሮ እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም አረንጓዴ ዐሻራቸውን እያኖሩ በዚያውም የኢትዮጵያን ልምድ እንደሚቀስሙ ጠቅሰዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ ዙሪያ የሚሠራ ሥራ ኢትዮጵያ የራሷን ቀጣናዊ ሚና እንድታጎለብት ያግዛል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ተመራጭ የሆነ ተሞክሮ እንዳላትና በዓለም ዓቀፍ ጉባዔዎችም ልምዷን እያካፈለች መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራን ወደሌሎች ሀገራት የማስፋፋት ሥራዋን በይበልጥ እንድታጠናክር ጠይቀዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት