ጽ/ቤቱ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝን የሚደግፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ሥራ አስገባ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ እና የአሠራር ሥርዓትን የሚደግፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አገልግሎት አስጀምሯል።
ጽሕፈት ቤቱ የሰው ኃይል እና የሀብት አሥተዳደር ሥርዓቱን ወጥ ለማድረግ የኢ አር ፒ፣ ዲጂታል የኮንፈረንስ አዳራሽ እና የመረጃ ማዕከልን ገንብቶ አስመርቋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ በዚሁ ወቅት፤ የፓርቲውን የአሠራር ሥርዓት በቴክኖሎጂ ማዘመን የተሞክሮ ማዕከልነቱን ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በሌሎች ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በቴክኖሎጂ ዘርፍ በመድገም፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን በፈር ቀዳጅነት ለመምራት እንደሚያግዝም አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሣሌት የማድረጉ ሥራ በመሰል ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ደግሞ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሞገስ ባልቻ ናቸው።
የስትራቴጂክ ጉዳዮች እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ የፓርቲውን አሠራሮች ቴክኖሎጂ መር የማድረግ ተግባሩ ወደ ሌሎች ክልሎች እንደሚስፋፋ ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም በድሬዳዋ ተግባራዊ እንደሚደረግ ነው ያመላከቱት፡፡
በሚኪያስ ዓለሙ