Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ለአምራቾች የሚሰጠውን አገልግሎት ማሳደጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክስዮን ማኅበር የሎጂስቲክስ አቅሙን በማሳደግ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚገኙ አምራቾች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አዳዲስ አሰራሮችን መጀመሩን ገልጿል፡፡

ተቋሙ የጀመራቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ለማስተዋወቅና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ያለመ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ማሳለጥ የሚቻልባቸውን አማራጮች በተመለከተ ሰፊ ውይይት መደረጉን በተቋሙ የግሎባል ሎጂስቲክስ ዳይሬክተር ወ/ሮ ምንተስኖት ዮሐንስ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን ለማግኘትና ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በሚፈለገው ጊዜ ከማድረስ አንጻር መዘግየት መኖሩን በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አምራቾች አንስተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት በገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚቸገሩ ገልጸው፤ ፈጣንና የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክስዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በመድረኩ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ተቋሙ ለከፍተኛ ምርት ላኪዎች አማራጮችን እያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የተናበበ የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን እውን ከማድረግ ባለፈ ቋሚ ቢሮዎችን በተመረጡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በመክፈት የሎጂስቲክስ አገልግሎቱን ማሳለጥ የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ የባቡር ቁጥሩን በመጨመር ዕለታዊ ምልልሶቹን ማሳደጉን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾች በሚፈልጉት ጊዜ የሎጅስቲክስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ለቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህል ላኪዎች የጭነት መጠን እስከ 25 ቶን ከፍ እንዲል አድርጓ ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከ20 ቶን በላይ ለሆኑ ምርቶች በእያንዳንዱ ቶን ይጠየቅ የነበረው ተጨማሪ ክፍያ እንዲቀር ጥያቄዎች መቅረባቸውን ወ/ሮ ምንተስኖት ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት ለቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህል ላኪዎች የጭነት መጠን ከ20 ወደ 25 ቶን ከፍ እንዲል በመደረጉ እስከ 25 ቶን ለሚደርሱ ጭነቶች ተጨማሪ ክፍያ እንደማይጠየቅ ነው ያስረዱት፡፡

ነገር ግን ከ25 ቶን በላይ ለሚሆኑ ምርቶች ከሚጠየቁት የ20 ቶን ክፍያ በተጨማሪ በእያንዳንዱ ቶን እንዲከፍሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.