Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የተሻለ መዳረሻ እየሆነች ነው – አምባሳደር ቼን ሃይ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም መስክ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኘው ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የተሻለ መዳረሻ እየሆነች ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ገለጹ።

የኢትዮጵያ እና የቻይናዋ ሺንቺያንግ ግዛት የቢዝነስ ትብብርና ልምድ ልውውጥ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በጉባኤው ላይ፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢኮኖሚ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት የላቀ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በቻይና አፍሪካ ትብብር ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና እየተጫወተች እንደምትገኝም ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማት፣ በአምራች፣ በግብርና እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች መስኮች ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ አኳያ የቻይና ሺንቺያንግ ግዛት ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

መንግሥት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው፤ ለኢንቨስትመንት የተሻለ መዳረሻ እየሆነች ነው ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

የቻይና ሺንቺያንግ ግዛት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተሳካ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲኖራቸው በኢትዮጵያ ያለው የቻይና ኤምባሲ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.