ሀገር አቀፍ የምግብ ጥራት ደረጃን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር አቀፍ የምግብ ጥራት ደረጃን በዚህ አመት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።
አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው የምግብ ምርቶች ከባለስልጣኑ ውጭ በሶስተኛ ወገን ሀገር አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ የሚያገኙበት አሰራር እየተተገበረ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ መሰረት ሀገር አቀፍ የምግብ ጥራት ደረጃ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የባለስልጣኑ የምግብ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ስሜ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
ለአብነትም የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት በንጥረ ነገር መበልጸግ እንዳለባቸው የሚያስገድድ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፥ ይህንን ሂደት ተከትለው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የጥራት ማረጋገጫ ምልክት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ አስገዳጅ ደረጃ የወጣባቸውን የምግብ ምርቶችን ከመግዛቱ በፊት እነዚህ ምልክቶች በማሸጊያዎች ላይ መስፈራቸውን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ተግባራዊ መደረጉ ለምግብ ደህንነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፥ የምግብ ምርት ለገበያ በሚቀርብበት ሂደት በሚፈለገው ልክ ጥራቱን ጠብቆ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የወተት ምርት ለገበያ በሚቀርብበት ሂደት በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈለገው ልክ ጥራቱን ጠብቆ ለህብረተሰቡ እየደረሰ አለመሆኑን በአብነት አንስተው፤ በፋብሪካ ሂደት ለሚያልፉ የወተት ምርቶች በተመሳሳይ የጥራት ማረጋገጫ ምልክት እየተሰጠ መሆኑን ነው አቶ ነጋሽ የገለጹት።
የጥራት ማረጋገጫ ምልክት ተግባራዊ የተደረገባቸው የምግብ ምርቶች የምግብ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፣ የገበታ ጨው፣ የታሸጉ ውሃዎች፣ ወተት፣ የለውዝ ቅቤና ለስላሳ መጠጦች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ
