የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችሉ የዲጂታል ሶሉሽኖች ይፋ ተደረጉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሥርዓት የተቀናጀ ነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት ሶሉሽን እንዲሁም ሀገር አቀፍ የትራፊክ ቅጣት ማዕከላዊ አስተዳደር ሥርዓትን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡
እነዚህም በሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርትና በነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያሉ ዘልማዳዊ የአሰራር ሂደቶችን ለማዘመንና በነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ረገድ ትክክለኛ ዳታ በወቅቱ ለማግኘት እንደሚያስችል ተገልጿል።
ደንበኞች በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አማራጮች መጠቀም እንዲችሉ፣ በትራፊክ ቅጣት አስተዳደር ግልጽነት ያለው አሰራርን ለማስፈንና የተገልጋዮችን እንግልት ለማስቀረት የላቀ ሚና ይኖራቸዋልም ተብሏል።
የዲጂታል ሶሉሽን ሀገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማግኘት ያሉ የሥራ ሂደቶች በቀላሉ ለማስተዳደር እና ለማቀላጠፍ የተዘጋጀ ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ሶሉሽን ሲሆን÷ ሚኒስቴሩ እስከ ትኬት መቁረጥ እና ዲጂታል ክፍያ ድረስ ወጥ የሆነ ሶሉሽን ለማቅረብ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የትራፊክ ሕጎች በተገቢው መንገድ እንዲተገበሩና በዲጂታል የታገዘ የትራፊክ ቅጣት አስተዳደርን በማስፈን በማዕከል ደረጃ ዳታ የሚመዘገብበትና በሀገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ የሆነ የትራፊክ አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አሰራር እንደሆነም ተመላክቷል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለውን ማኑዋል የትራፊክ ቅጣት አሰራርን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጂታል በመቀየር ውጤታማ ያልሆነ የሀብት አጠቃቀም ለመቅረፍና ፖሊሲዎችን ለማውጣት የመረጃ እጥረት ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታልም ነው የተባለው፡፡
ሥርዓቶቹ በግል ሶፍትዌር አልሚ ተቋማት የለሙና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አማራጮች ከኢትዮ ቴሌኮም ሥርዓቶችና ከቴሌብር ጋር በኤፒአይ በቀላሉ እንዲዋሄዱ በማድረግ በጋራ የመሥራት አቅምን በማሳደግ የሥራ ፈጠራንና አካታች የዲጂታል ሥነምህዳርን ማጠናከር የቻለ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ አመላክቷል።