ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በአማራ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚያስችሉ ጉዳዮች ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክሩ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዳሉት÷ በግጭት ወቅት ተፋላሚ ኃይሎች ብቻ ሳይሆን ሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት የሚደርስ መሆኑን በመረዳት የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ሲሠራ ቆይቷል።
ወደ ሰላም የገቡ ታጣቂ ኃይሎችን የክልሉ መንግሥት ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተሐድሶ ሥልጠና በመሥጠት ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።
አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸው÷ በቀጣይ የተሐድሶ ሥልጠናውን ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ይደረጋል ብለዋል።
የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ኑሮ ተመልሰው የልማት አቅም እንዲሆኑ ኮሚሽኑ በሚያደርገው ጥረት የክልሉ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ አጋር አካላትም ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች የቀድሞ ታጣቂዎችን በማሠልጠን እና መልሶ በማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የመንግሥት መዋቅር ለኮሚሽኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን አሚኮ ዘግቧል።