Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ19 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል ፈተና እየተዘጋጁ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል 19 ሺህ 127 ተማሪዎች ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየተዘጋጁ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዘንድሮ ሀገራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የክልሉ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የማዘጋጀት ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ነው፡፡

በዚህም ፈተናው በኦንላይንና በወረቀት የሚሰጥ በመሆኑ ለተማሪዎች አዲስ እንዳይሆን የተግባር ልምምዶች በየትምህርት ቤቶች እየተሰጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ የሚፈተኑ መሆናቸውን አንስተው÷ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለው የትምህርት ይዘት በተገቢው እንዲሸፈን ለ13 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎች ልዩ የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህም ተፈታኞቹ የራስ መተማመናቸውን በመጨመር የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያስችላል ብለዋል።

ባለፈው የትምህርት ዘመን በርካታ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን አለማሳለፋቸውን አስታውሰው÷ ይህ ሁኔታ ዘንድሮ እንዳይደገም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በመለየት ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ የግል ተፈታኝ የሆኑ ከ3 ሺህ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን ጨምሮ 19 ሺህ 127 ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተናው እንደሚቀመጡ አመላክተዋል።

የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቂያ ፈተና ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ማሳወቁ ይታወሳል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.