ሚዲያዎች ፈጣን እና ጊዜውን የዋጀ መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ ይገባቸዋል – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች የአብሮነት ትርክቶችን ለመገንባት ፈተና እንዳይሆኑ ሚዲያዎች ፈጣንና ጊዜውን የዋጀ መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው ምሁራን ገለጹ።
ሀሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር የህዝቦች አንድነትና የጋራ እሴቶችን በመጠበቅ ሂደት ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመው÷ አለመቻቻል ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ ቁርሾ እንደሚያስከትልም አስገንዝበዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች እና ሀሰተኛ መረጃዎች እየተባባሱ መምጣታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የስጋት ምንጭ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት መምህር እና የሚዲያ አማካሪ አየለ አዲስ (ዶ/ር)÷ ብሔር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካዊ አመለካከት መሠረት ተደርገው የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች ብሔራዊ አደጋ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር አስናቀ እንድርያስ በበኩላቸው÷ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና በዚያውም ልክ ጉዳቱ እየከፋ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡
በተለይ ከማኀበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር በተገናኘ ሀሰተኛ መረጃ በስፋት እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሀሰተኛ መረጃና ጥላቻ ንግግር ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር እንደሆነም አንስተዋል።
ይህንንም ለመከላከል ሚዲያዎች እውነታን የሚያሳዩ ፈጣን እና ጊዜውን የዋጀ መረጃ ለማህበረሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸው ምሁራኑ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል።
ማንኛውም መረጃ ትክክል ነው ብሎ ከመቀበል ሀቅን ማጣራትና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ ማድረስ እንዲሁም ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸውን መረጃዎች በወቅቱ በማቅረብ መስራት እንደሚያስፈልግ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በአስጨናቂ ጉዱ