ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ ልማት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ዲጂታል መሰረተ ልማትን እያስፋፋች ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ለሁለንተናዊ ልማት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ዲጂታል መሰረተ ልማትን እያስፋፋች ነው ሲሉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ገለጹ።
በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ ቴክኖሎጂ አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባትና አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የማይተካ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታውን በመገንዘብና ቴክኖሎጂ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት ያለውን ፋይዳ በመረዳት ዲጂታል መሰረተ ልማትን እያስፋፋች መሆኗን አስታውቀዋል።
ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠና ኢኒሼቲቭ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል የማስገባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ቁልፍ የዲጂታል መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ዜጎች ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብታቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ኤክስፖው እንደ ሀገር ብሎም እንደ አህጉር ቴክኖሎጂን ማዕከል አድርገው የተሰሩ ስራዎችና የዕድገት ደረጃውን በተመለከተ የሚመከርበትና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦች የሚፈልቁበት መሆኑን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ የሳይበር ደህንነት ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ቁልፍ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የሳይበር ደህንነት ካውንስል ሊቀ መንበር መሃመድ አልኩዋቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ብሔራዊ ደህንነትንና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ላይ ሀገራት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።