ሃማስ ከእስራኤል ጋር ያቋረጠውን ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሃማስ ከእስራኤል ጋር አቋርጦት የነበረውን የዶሃ ድርድር ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሃማስ ፈቀደኝነቱን የገለጸው እስራኤል በአዲስ መልኩ በቡድኑ ላይ መጠነ ሰፊና የተጠናከረ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
እስራኤል የቀሩ ታጋቾችን ለማስለቀቅ በሚል በጀመረቸው ወታደራዊ ዘመቻ በ150 የቡድኑ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተሰምቷል፡፡
ከእስራኤል የቀናት ጥቃት በኋላም በኳታር ዶሃ የሚገኘው የሃማስ ተዳራዳሪ ልዑክ ከእስራኤል ጋር ቀደም ሲል ያቋረጠውን ንግግር ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
የእስራኤል ተደራዳሪ ልዑክም የሃማስ ልዑክ ያሳየውን ፈቃደኝነት ተከትሎ ዛሬ ምሽት ወደ ኳታር እንደሚያቀና ተመላክቷል፡፡
ቀጥተኛ እንዳልሆነ የተነገረለት የዶሃው ድርድር ከወትሮው በተለየ ተስፋ ባይጣልበትም ፤ ሁለቱን ወገኖች ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊወስድ እንደሚችል መጠቆሙን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡
በመጀመሪያ ዙር በተደረገው ድርድር ሃማስ ቀሪ 58 ታጋቾችን ለመልቀቅ በእስራኤል የቀረበውን ሃሳብ ባለመቀበሉ አስራኤል በቡድኑ ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ መቀጠሏ የሚታወስ ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ