ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል ወንጀልን ለመከላከል ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) እየተበራከተ ያለውን ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል የሚፈጸም ወንጀልን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ
ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተዘጋጁና ሆን ተብሎ ከባዕድ ነገር ጋር የተቀላቀሉ የምግብ ምርቶችን ለገበያ የማቅረብ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ባለስልጣኑ ገልጿል።
ከምግብ ምርት ጋር የተገናኙ ወንጀሎችን ለመከላከል የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን በባለስልጣኑ የምግብ ኢንስፔክሽንና የህግ ማስፈጸም ስራ አስፈጻሚ ሙላቱ ተስፋዬ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ዘመናዊ የምግብ መመርመሪያ መሳሪያዎችን በመጠቀም ወደ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን እንደሚቆጣጠር ገልጸዋል።
በዝግጅት ወቅት በጥንቃቄ ጉድለት ከሚፈጠረው የምግብ ጥራት ችግር ባሻገር ሆን ብለው ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት ባዕድ ነገሮችን ከምግብ ጋር የሚቀላቀሉ አካላት መኖራቸውን ነው ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።
ህገወጥ የምግብ ማምረቻ ቦታዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ይህንን የሚያደርጉ አካላትን ለህግ በማቅረብ በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል።
በምግብና የመድሃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/2011 የወንጀል ቅጣትን የሚመለከተው አንቀጽ 67 በምግብ ላይ የሚሰሩ ወንጀሎች እስከ 20 አመት ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጡ ይደነግጋል።
በኃይለማርያም ተገኝ