መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በአጭር ዓመታት ውስጥ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በአጭር ዓመታት ውስጥ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ዳይሬክተር ሳምሶን ዓይናቸው፥ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች ከተማዋን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል፡፡
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተደረገባቸው አምስቱ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም መሆኑን አስታውሰው÷ ይህም ቱሪዝም እንደማኅበራዊ ዘርፍ ሲታይ ከነበረበት ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ በመወሰድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በከተማዋ የተከናወኑ ሜጋ የቱሪዝም መዳረሻ ፕሮጀክቶች ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ማሳያ እንደሆኑ ጠቁመው÷ አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን ማስቻላቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 84 የሚጠጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች በአዲስ አበባ መካሄዳቸውን ጠቅሰው፥ ለዚህም በከተማዋ የተገነቡ ትላልቅ የስብሰባ ማዕከላት አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም የዓድዋ ሙዚየም፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከልና የቤተመንግሥት ሙዚየምን አንስተዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም በከተማዋ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲጨምር ከማስቻሉ ባሻገር፥ የውጭ ሀገራት ተሳታፊዎች በከተማዋ ያሉ የቱሪዝም መስህቦችን በመጎብኘት ለሌሎች እንዲያስተዋውቁ ዕድል መፍጠሩን አመላክተዋል።
በጂኦ ቱሪዝም ረገድ በየአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ገጸ በረከት ከማኅበረሰቡ ባህል ጋር በማስተሳሰር የማስተዋወቅ ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የማስተሳሰር ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው÷ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሰማሩ ተቋማት ባለሙያዎች የሥራ ላይ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ÷ በየአካባቢው ሀገርን እንወቅ የሚሉ ክበባትን የማጠናከር ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ9 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች አዲስ አበባን እንደጎበኙና የቱሪዝም ቦታዎችን የማስተዋወቅ ሥራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
በአድማሱ አራጋው