Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፋንታ ጭምር የሚወስን ነው  – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፋንታ የሚወስን ጉዳይ ነው ሲሉ የታሪክና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ ስህተቶችን የሚያርም ውሳኔ በመሆኑ የተጀመሩ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ምሁራኑ አስገንዝበዋል፡፡

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪ አብዱ መሐመድ (ዶ/ር)፥ መንግሥት የጀመረው የባሕር በር የማግኘት ጥረት አካባቢያዊ መረጋጋት የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቀጣናው አለኝ የምትለው የባለቤትነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ በር የሚከፍት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በተሳሳተ ትርክትና ሴራ ከቀይ ባሕር ተጠቃሚነት መገለሏን አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይም ኢትዮጵያ ለዘመናት አጥታው የቆየችውን የባሕር በር ተጠቃሚነት ዳግም ለማግኘት እያደረገች ያለው እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት እየተከተለ ያለው የዲፕሎማሲ አካሄድ ሀገሪቱ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግና የዘመናት ጥያቄ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ አንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡

መንግሥት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ቁጭት ፈጥሮ የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ በመመለስና ስብራትን በመጠገን ታሪካዊ ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የመንግስትን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመደገፍ ዜጎች የውስጥ አንድነትንና ሰላምን በመጠበቅ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ምሁራኑ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡

በኢብራሂም ባዲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.